በክልሉ ከታችኛው እርከን ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከታችኛው እርከን ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል
ባህርዳር፤ ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን በምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገለፁ።
በባህርዳር ከተማ በ28 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የመስከረም16 የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል።
በምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት ላይ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በሁሉም ቀበሌዎች አንድ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለመገንባት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናገረዋል።
ከፓርትነርስ ኢን ኢዱኬሽን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በባህር ዳር ከተማ በመስከረም 16 1ኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ሞዴል የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ መጠናቀቁ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ወደፊትም ባለሃብቶችን፣ ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማስተባበር የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የመገንባቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልፅግና መሰረት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ሁኔታ የመፍጠሩ ተግባር ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በባህርዳር ከተማ በ28 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የመስከረም16 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለሌሎች ሞዴል ነው ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሏለም አቤ (ዶ/ር) ናቸው።
ትምህርት ቤቱ 14 የመማሪያ ክፍሎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ያሉትና የውስጥ ቁሳቁስ የተሟላለት መሆኑን ተናግረዋል ።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቱ 760 ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።
የፓርትነርስ ኢን ኢዱኬሽን ኢትዮጵያ ቦርድ ሰብሳቢ ሚስተር ቴሬንስ ሂላቢ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የትምህርትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።