በሰላምና በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የበደልነውን ህዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በሰላምና በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የበደልነውን ህዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል
ደብረብርሃን፤ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፡-በሰላምና ልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበደልነውን ህዝብና መንግስት ለመካስ ተዘጋጅተናል ሲሉ በሰሜን ሸዋ ዞንና በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።
በአማራ ክልል በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን ተቀብለው ወደ ቀደመ ህይወታቸው እየተመለሱ መሆኑም ተመላክቷል።
በሰሜን ሸዋ ዞንና በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች በደብረ ብርሃን የስልጠና ማዕከል ዛሬ የተሀድሶ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።
ከተመላሾቹ መካከል ከምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የመጣው ፈለቀ ሰጤ በተሳሳተ መንገድ በመጓዝ በህዝብ ላይ ባደረሰው በደልና ጥፋት መጸጸቱን ተናግሯል።
ትግሉ የህዝብን ሃብትና ንብረት በመዝረፍ ለመበልጸግ ያለመ መሆኑን በመገንዘቤ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብዬ ወደሰላም ተመልሻለሁ ብሏል።
ስንፈጽመው በነበረው የጥፋት ተግባር ህብረተሰቡን ከመበደል ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው በመስተጓጎሉ ለጸጸት መዳረጉን ገልጾ፣ ከተሀድሶ ስልጠና በኋላ ህዝቡን ለመካስ እንደሚሰራ ተናግሯል።
ከባሶና ወራና ወረዳ የመጣው ተስፋዬ ጌታቸው በበኩሉ፥ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማወክ ባደረስኩት በደል በመጸጸትና የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ተመልሻለሁ ብለዋል።
አሁንም ጫካ ቀርተው በጥፋት ተግባራቸው የቀጠሉት ትምህርት እንዲቋረጥ፣ንጹሀን እንዲገደሉ በማድረግ የሚመለስ የፖለቲካ ጥያቄ እንደሌለ ተገንዝበው ወደሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
በቀጣይ በየአካባቢው በሚከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ ጉልህ አስተዋጾ በማድረግ የበደሉትን ህዝብና መንግስት ለመካስ ዝግጁነታቸውንም አረጋግጠዋል።
ከቡልጋ ከተማ አስተዳደር የመጣው ሙሉቀን መስፍን በበኩሉ፥ ትግሉ የአማራን ህዝብ ጥያቄ የሚያስመልስ ሳይሆን የጥቂቶች ሀብት ማከማቻ እየሆነ መምጣቱን በመገንዘብ የመንግስትን የሰላም አማራጭ መቀበሉን ተናግሯል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ደጀኔ ልመንህ እንዳሉት፥ ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት ከህዝብ ጋር የተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ውጤት እያስገኙ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን ጥሪ ተቀብለው ወደ ቀደመ ህይወታቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቁመው፣ ለተመላሾቹ የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት በፈለጉት የሙያ ዘርፍ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
አሁንም በጫካ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሀይል የሚመለስ ምንም አይነት ጥያቄ እንደማይኖር በመረዳትና የጥፋት ተግባራቸውን በመተው የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ አስገንዝብዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው፥ በዞኑ የሰፈነው ሰላም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንዲሻሻል መልካም እድል ፈጥሯል ብለዋል።
መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተመለሱ ወንድሞች አሁንም ሳይመለሱ በጫካ ያሉ ታጣቂዎችን መክረው ወደሰላም እንዲመለሱና የበደሉትን ህዝብ እንዲክሱ የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደርና በዙሪያው እየሰፈነ ያለው ሰላም ለኢንዱስትሪና ለንግድ ሥራዎች መስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።
ወደሰላም የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን በቀጣይ በሚፈልጉት የሥራ ዘርፍ ለማሰማራት በአስተዳደሩ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።