የስፖርት ቱሪዝም መጠናከር ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መነቃቃት ፋይዳው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ቱሪዝም መጠናከር ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መነቃቃት ፋይዳው የጎላ ነው
ደብረብርሃን ፤ጥር 3/2018 (ኢዜአ) ፡- ስፖርት ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር የአካባቢውን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ አለው ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በደሉ ውብሸት ገለጹ።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 2018 የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ዛሬ በደብረብርሃን ከተማ ተካሂደዋል።
ውድድሮቹም የ6 ኪሎ ሜትር የሴቶችና ወንዶች ሩጫ እና የ22 ኪሎ ሜትር የዱላ ቅብብልን ያካተተ ነው።
የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በእለቱ እንደገለጹት ስፖርት ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር ለአካባቢው ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ምርታማነት እድገት የጎላ ፋይዳ አለው።
በተጨማሪም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ስፖርተኞችንና ተመልካቾችን በማገናኘት ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በደብረ ብርሃን የተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያም የከተማዋን እድገት፣ የመስህብ ስፍራዎችና ጸጋዎችን ለማስተዋወቅ መልካም እድል የሚፈጥር በመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ቡድን መሪ አቶ አክሊል ጌታቸው እንዳሉት ከተማዋ ያላት የአየር ንብረት ለስፖርታዊ ውድድሮች አመቺ ነው።
ዛሬ የተካሄደው የስፖርት ውድድርም ወንድማማችነትን ለማጠናከርና ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ በመሆኑ አዘጋጆቹን አመስግነዋል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ሀላፊ ወይዘሮ ሃና ገብረስላሴ በበኩላቸው ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ህፃናትን፣ ወጣቶችንና ታዋቂ አትሌቶችን ያሳተፈ ውድድር መካሄዱን ገልጸዋልⵆ
ውድድሩም የ6 ኪሎ ሜትር የሴቶችና ወንዶች ሩጫ እና የ22 ኪሎ ሜትር የዱላ ቅብብልን ያካተተ እንደነበር አንስተዋል።
በ6 ኪሎ ሜትር የወንዶች ሩጫ ውድድር 1ኛ የወጣው ስጦታው ሰማኸኝ እንዳለው እንደዚህ ያለ ውድድር ያልታወቁ አትሌቶች የሚታዩበት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።