በአፋር ክልል ከለውጡ ዓመታት ወዲህ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የክልሉን የመልማት አቅምን ያሳዩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ከለውጡ ዓመታት ወዲህ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የክልሉን የመልማት አቅምን ያሳዩ ናቸው
ሰመራ፣ጥር 3/2018(ኢዜአ)፦በአፋር ክልል ከለውጡ ዓመታት ወዲህ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የክልሉን የመልማት አቅም ማሳየት የቻሉ መሆናቸውን በብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ተናገሩ።
በብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ አመራሮች በክልሉ በሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደርና በዱብቲ ወረዳ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በወቅቱ እንዳሉት፥ በአፋር ክልል ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
የልማት ስራዎቹ የክልሉን የመልማት አቅም ያሳዩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአዋሽ ወንዝን ለመስኖ አገልግሎት እንዲውል በማድረግ ሰፋፊ እርሻዎች መሠራታቸውን መመልከታቸውን ገልጸው፤ በተለይም በዱብቲ ወረዳ እየለማ ያለው የስንዴና የሱፍ ምርት አስደናቂ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃግብር በተለይም በዶሮ፣እንቁላል፣ በዘመናዊ ከብት እርባታ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ክልሉ የብልፅግና ተስፋ የሚታይበት መሆኑን የገለፁት አቶ ፍቃዱ፤በሠመራ ከተማ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማትም የህብረተሰቡን ባህልና እሴት መሠረት ያደረገ፣ከተሜነትን ያዋሃደና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ወይዘሮ ማርታ ወይቤ በበኩላቸው፥ በክልሉ የተሰሩ ስራዎች ከዚህ ቀደም ስለ በረሃ የነበረውን አመለካከት ጭምር የቀየሩ ናቸው ብለዋል።
በተለይም የሠመራ ከተማ ኮሪደር ልማት ባህላዊ ይዘቱን የጠበቀ፣ማራኪና ከተማዋን እያንሰራሩ ከሚገኙ ከተሞች ተርታ እንድትመደብ የሚያደርጋት መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ በለውጡ ዓመታት የታዩ ተግባራት የሀገሪቷን ማንሰራራትና እመርታዎችን ያንፀባረቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፥ በአፋር ክልል ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም የብልፅግናን መንገድ የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የህዝብ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረጉ ስራዎች በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ እየተሰሩ መሆናቸውን ተመልክተናል ብለዋል።
"ጠንካራ አደረጃጀት ለጠንካራ ፓርቲ" በሚል መሪ ሀሳብ በብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 የ6 ወራት አፈፃፀም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ መድረክ ትናንት በሰመራ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።