በሀላባ ዘመን መለወጫ በዓል ያሉትን የአብሮነትና የእርስ በርስ ትስስር እሴቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በሀላባ ዘመን መለወጫ በዓል ያሉትን የአብሮነትና የእርስ በርስ ትስስር እሴቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ቁሊቶ፣ ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፡-የሀላባ ዘመን መለወጫ በዓል "ሴራ" ሲከበር ያሉትን የአብሮነት፣ የመረዳዳትና የእርስ በርስ ትስስር እሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ መሆን እንዳለበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
"ሴራ በዓላችን በህብረት የመቻል አቅም ማሳያችን" በሚል መሪ ሀሳብ የሀላባ የዘመን መለወጫ በዓል "ሴራ" በተለያዩ ክዋኔዎች ዛሬ በሀላባ ስታዲየም ተከብሯል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ ሲከበር ያሉትን የእርስ በርስ ትስስርና የአብሮነት እሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የ"ሴራ" በዓል ከልዩነት ይልቅ አብሮነትና እርስ በርስ መደጋገፍን ለማጠናከር የሚያግዙ እሴቶች እንዳሉት ጠቅሰው፣ በዓሉ ከሃላባዎች ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ጋር የተሳሳረ መሆኑንም አመልክተዋል።
የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልመሀዲ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚረዱ በርካታ እሴቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
የሀላባ የዘመን መለወጫ በዓል "ሴራ" የአብሮነት፣ የመረዳዳትና የመተሳሰብ እሴት ጎልቶ ከሚንፀባረቅባቸው ባህሎች አንደኛው መሆኑን ጠቅሰው፣ የበዓሉ መከበር እነዚህን ማህበራዊ እሴቶች አጠናክሮ ላማስቀጠል ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የቤተሰብ ኃላፊነትንና የሥራ ድርሻን በአግባቡ መወጣት ጭምር የሚያስተምር በመሆኑ ለልማታዊ እንቅስቃሴ አበርክቶው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
የበዓሉን እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ሚኒስቴሩ የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን በበኩላቸው ሀላባ የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባህልና የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች እንዳሉት አንስተዋል።
የዘመን መለወጫ "ሴራ" በዓል በታህሳስ ወር መጠናቀቂያ እና በወርሃ ጥር መግቢያ እንደሚከበርም ነው የተናገሩት።
በዓሉ በሃላባዎች ዘንድ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ መሆኑን ጠቁመው፣ ለአቅመ አዳም የደረሱ ወጣቶች ራሳቸውን ለማስተዳደር ወደ ድርብ ኃላፊነት የሚሸጋገሩበት መሆኑንም አመልክተዋል።
"ሀላባ ተከባብሮና ተደማምጦ በጋራ ለመልማት የሚረዱ በርካታ እሴቶች አሉት" ያሉት ደግም የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ አሚና ኢሳ ናቸው፡፡
ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የሀላባ ዘመን መለወጫ በዓል የአብሮነት እሴት የሚጎላበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዓሉን ከሌሎች ወንድምና እህት ህዝብች ጋር በአብሮነት በማክበራቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በበዓሉ አከባበር ሥነ ስርዓት ላይ ከፌዴራልና ከክልሉ የመጡ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡