የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማረጋገጥ የባህር በር ወሳኝ ነው-የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማረጋገጥ የባህር በር ወሳኝ ነው-የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ጥር 3/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማረጋገጥ የባህር በር ማግኘት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት የመላው ኢትዮጵያውያንን ልብ ያደማ የማይረሳ ጠባሳ መሆኑን አመራር አባላቱ ተናግረዋል፡፡
የባህር በር ባለቤትነት የረጅም ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድን፣የትውልድንና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ከፍታ ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ የተጀመሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ጠቅሰዋል፡፡
የአገው ለፍትህና ለዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አዲሱ መኮንን (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ሴራ የባህር በር ያጣችበት ሂደት የሚያስቆጭ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህር በር ለአገር እድገት የጀርባ አጥንት መሆኑን አንስተው፤ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት መፍጠሩን ተናግረዋል።
የባህር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለስኬቱ በጋራ እየተረባረበ መሆኑን አመልክተዋል።
የራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ከበደ በበኩላቸው እንደገለጹት፤የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማረጋገጥ የባህር በር ማግኘት ዋነኛ መሰረት ነው ብለዋል፡፡
የባህር በር ጉዳይን ዓለም አቀፍ አጀንዳ በማድረግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚደነቁና የሚደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማስተናገድ የባህር በር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አሰፉ ተረፈ በበኩላቸው፤ የባህር በር ጉዳይ የሁላችንም ጥያቄ በመሆኑ በጋራ እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በዚህ ረገድ መንግስት የጀመረው ጥረት ግቡን እንዲመታ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሚና ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀ መንበር ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት የኢትዮጵያውያንን ልብ በእጅጉ ያደማ የታሪክ ጠባሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን የባህር በር ያጣችበት ሂደት ኢ-ፍትሃዊ መሆኑን አንስተው፥ አሁን ላይ ጉዳዩ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ ሁሉም የበኩሉን ማድረጉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።