ቀጥታ፡

በክልሉ በሰፈነው ሠላም ልማትን የማጠናከር ሥራ ይቀጥላል

አሶሳ፤ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰፈነውን ሠላም በመጠቀም ልማትን የማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ምክር ቤት ከመንጌ ወረዳ መስተዳድር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት "የህዝብ ለህዝብ ትስስር መድረክ" በመንጌ ወረዳ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፤ በክልሉ የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህዝበ ለህዝብ ትስስር መድረኩ በክልሉ የሰፈነውን ሠላም ለማጽናትና አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ክልሉ የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ልማት በመቀየር የዜጎችን ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ በልማት ስራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ በማጠናከር ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ መትጋት ይጠበቅበታል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ በበኩላቸው፤ የህዝቦችን ትስስር ማጠናከር ለጋራ ዓላማ እንዲቆሙ የሚያደርግ እና የዜጎችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ተመሳሳይ መድረኮችን በማዘጋጀት ህብረተሰቡ ክልላዊ እና ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲይዝ ይደረጋል ነው ያሉት።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ለዘላቂ ሠላም እና አብሮነት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር ናቸው።


 

የመደመር መንግስት ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን በማድመጥ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረው ህብረተሰቡ የልማት ስራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የመንጌ ወረዳ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም