የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የትውልዱ አጀንዳ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የትውልዱ አጀንዳ ነው
ሀዋሳ፤ጥር 3/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የትውልዱ አጀንዳ ሆኖ የሚቀጥልና የሀገር የህልውና ጉዳይ መሆኑን የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡
ለብዙ ዘመናት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ምክንያቱ በግልጽ በማይታወቅ መልኩ ለዓመታት የባህር መግቢያና መውጫ የተቆለፈባት ሀገር ሆናለች።
በአሁኑ ወቅት ከ120 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ላላት ሀገር የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከገቢና ወጪ ንግድ ባለፈ የሀገርን ህልውና የሚወስን የትውልድ ጥያቄም ጭምር ሆኖ በስፋት እየተነሳ ይገኛል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የትውልዱ አጀንዳ ሆኖ የሚቀጥል የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ደምሴ ሱካሬ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት ሁኔታ ለህዝብ ግልጽ ያልሆነና ቁጭት ፈጥሮ የቆየ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል።
የነበራትን የባህር በር አጥታ በዝምታ ዓመታት አልፈው በአሁኑ ወቅት ትውልዱ ጥያቄውን በይፋ እያነሳና ተገቢ ምላሽ የሚጠብቅ ሀገራዊ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከምጣኔ ሀብት፣ከፖለቲካ፣ ከዲፕሎማሲና ቀጣናዊ የልማት ትስስር ባለፈ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው ግድ ይላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና በህልውናዋ ጉዳይ በተቃራኒ ሊቆም የሚችል ዜጋ መኖር እንደሌለበት አንስተው፥ ፓርቲያቸው በዚህ ረገድ የጸና አቋም ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ በለጠ ሲጌቦ፤ የባህር በር ጉዳይ በአደባባይ ከመነሳቱ ባለፈ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር እንዲገነዘበው መደረጉ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ጥያቄው ተገቢ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ የትውልዱ ጥያቄ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ተስፋዬ ኤርሚያስ፤ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ እንዲያገኝ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን እያደገ የመጣውን ህዝቧን ለመመገብ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ለመሆንና ብሔራዊ ደህንነቷን ለማስጠበቅ ጭምር መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊያገኝ ግድ ይላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ተቆልፎባት መኖር የማትችል መሆኑን ዓለም እንዲገነዘበው መደረጉን አንስተው፥ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ጥረቱ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።