በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተከናወኑ ተግባራት ሀገር ወደተሻለ ከፍታ እንድታመራ መሰረት ጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተከናወኑ ተግባራት ሀገር ወደተሻለ ከፍታ እንድታመራ መሰረት ጥለዋል
ወልቂጤ፤ ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፡-በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ወደተሻለ ከፍታ እንድታመራ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ስትራቴጂው በቅርቡ ይፋ የተደረገውን ዲጂታል 2030 ትግበራን ለማሳካት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም ምሁራኑ ጠቁመዋል።
መንግስት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በየዘርፉ የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ ለማዘመንና ለማሳለጥ በቅርቡ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተተገበሩ ቴክኖሎጂዎች ሀገሪቱ ወደተሻለ ከፍታ እንድታመራ መሰረት የጣሉ ናቸው።
ዲጂታል ቴክኖሎጂው በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርትና በፋይናንስ ዘርፎች ያመጣው ተጨባጭ ለውጥና ያስገኘው ጥቅም እያደገ መሆኑን የተናገሩት በዩኒቨርሲቲው የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ መምህር በላይ አለምነህ ናቸው።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬቶች በዘርፉ ልምድና ተሞክሮ የተቀሰመበት መሆኑን ገልጸው፣ በስትራቴጂው በተዘረጉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች በተለያዩ ተቋማት ከወረቀት ነጻ የሆነ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲውም የትምህርት መርሃ ግብሮችና በሥራ ክፍሎች የመረጃ ልውውጥ ሥራው ከወረቀት ነጻ በሆነ መንገድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዞ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በመደረጉ ተማሪዎች ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው ትምህርታቸውን በኦንላይን መከታተል መቻላቸውን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ጋር የሚያደርገው ግንኙነትና የተማሪዎች ውጤትም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ መደረጋቸውንም ነው ያመለከቱት።
የመማር ማስተማር ሂደቱን በማዘመንና የፈተና አሰጣጥ ሥርአቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የፈተናን ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት በቅርቡ ይፋ ለተደረገው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ መሰረትና ግብአት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኔትዎርኪንግ ሳይበር ደህንነት መምህር ወንድወሰን ዝና በበኩላቸው ለተማሪዎች በሳይበር መረጃ ደህንነት አጠባበቅ ላይ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠትና በቂ ዕውቀት ለማስጨበጥ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 አበርክቶ ላቅ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ይበልጥ መረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፣ "ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዲጂታል ቴክኖሎጂ ያሉ አማራጮችን በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል" ብለዋል።
ስትራቴጂው ዜጎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮች ታግዘው ባሉበት ቦታ ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መሆን እንደሀገር ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ከመከላከል ባለፈ የተለያዩ ማጭበርበሮችን ለማስቀረትም እያገዘ ነው።
ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ አካታችና ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ በሁሉም ዘርፍ ተግባራትና የሚሰጡ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙና ቀልጣፋ እንዲሆኑ የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም መምህሩ ገልጸዋል።