ቀጥታ፡

በድሬደዋ አስተዳደር የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ስራ ተጀመረ

ድሬደዋ፣ጥር 3/2018(ኢዜአ) ፡-በድሬደዋ አስተዳደር 38ቱ የገጠር ቀበሌዎች የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ዛሬ መካሄድ ጀመረ።

በአስተዳደሩ አራቱ የገጠር ክላስተሮች ዛሬ በተጀመረውና ለአንድ ወር በሚዘልቀው የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ሥራ 5ሺህ 550 ሄክታር የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት እንደሚከናወን ታውቋል።

በአሰሊሶ ገጠር ክላስተር ገንደ ሪጌ ቀበሌ ተገኝተው የተፋሰስ ልማቱን ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የአስተዳደሩ ምክርቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ከሪማ አሊ ናቸው።


 

የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ አብዲ ሙክታር፣ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተቀሩት ክላስተሮች ተገኝተው የተፋሰስ ልማቱን አስጀምረዋል።

"የተቀናጀ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት፤ ለግብርና  ሽግግር ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ በተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ላይ የተለያዩ የአፈርና የውሃ ሃብትን በዘላቂነት መጠበቅና ማበልፀግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚካሄዱም በወቅቱ ተገልጿል።


 

ለአንድ ወር በሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራው ከ37ሺህ 900  በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም