ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና ጥገና ተከናውኗል

ገንዳውኃ፣ ጥር 3/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ የተከናወነው የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና ጥገና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ማገዙን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አያና ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህም ህብረተሰቡንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተሰራው ስራ የ108 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና የ264 ክፍሎች ጥገናን ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል። 

ለግንባታና ጥገና ስራውም ከህብረተሰቡ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው ከከተማና ወረዳ አስተዳደሮች እንዲሁም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

በአዲስ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የመማሪያ ክፍሎችም ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ከመማሪያ ክፍሎቹ በተጨማሪ የመፀዳጃ ቤት፣ የመምህራን መኖሪያ ቤቶችና የአጥር ግንባታ ስራን ማካሄድ መቻሉን ገልጸዋል። 

በዞኑ የገንዳውኃ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በየነ አዳነ እንዳሉት፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። 

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ 12 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል። 

 ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የትምህርት ቤት አጥር፣ መፀዳጃና የቤተ ሙከራ ግንባታ መሰራታቸውን ጠቁመው ይሄም የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ ያለመ ነው ብለዋል። 

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ውጤታማ የመማር ማስተማር ስራ እንዲኖር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመተማ ከተማ የጉድኝት ሱፐርቫይዘር ፈቃዴ ከፍያለው ናቸው። 

የመማሪያ ክፍሎች ጥራቱን የጠበቀ ሆነው መገንባታቸውን ጠቁመው በከተማዋ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም በግንባታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

 በዞኑ 240 የ1ኛ ደረጃና 10 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም