በክልሉ የተለያዩ ከተሞች 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተለያዩ ከተሞች 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው
ባህር ዳር፤ ጥር 3/2018(ኢዜአ):-በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው አማካሪ አቶ ሽቤ ክንዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የኮሪደር ልማት ሥራው የከተሞችን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለኑሮ ምቹና ተወዳዳሪነታቸው ከፍ እንዲል እያደረገ ነው።
ባለፉት ጊዜያት የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋት በዚህ ዓመት በስምንት ዋና ዋና ከተሞችና በ20 መካከለኛና አነስተኛ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ24 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድን ጨምሮ የእግረኛ፣ የብስክሌትና ሌሎችን መሰረተልማቶችን ያካተተ የኮሪደር ልማት ለማከናወን ተችሏል።
በተጨማሪም በከተሞች ልማቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ የህፃናት መጫዎቻ፣ አደባባዮችና ሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎችን አካቶ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ለልማት ስራው ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1ነጥብ 8 ቢሊዮን የሚሆነው ከህብረተሰቡ በድጋፍ የተገኘ መሆኑን አንስተዋል።
በልማት ሥራው አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ወገኖች የሥራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
በባህር ዳር ከተማ ሦስተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ መጀመሩን እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞችም አንደኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠናቆ ሁለተኛው ምዕራፍ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው ቀደም ሲል በልማት ወደኋላ ቀርተው የነበሩ ከተሞችን ደረጃቸውን በጠበቀ አግባብ እንዲገነቡ ለማድረግ ማስቻሉንም አስገንዝበዋል።
ለአረንጓዴ ቦታና ለመዝናኛ ስፍራ ትኩረት ሰጥቶ እየተከናወነ በመሆኑ የከተሞች ገጽታ እየተቀየረ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ከተሞች በፕላን እንዲመሩ፣ ለኑሮ የተመቹ እንዲሆኑ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ የቱሪዝም ሳቢነታቸውን በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው በጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተመራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ልማቱ የህብረተሰቡን የሥራ ባህል በማዳበር ኑሮውን በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።
በቀሪ ወራትም ዕቅዱን በተሟላ መንገድ ለማከናወን የአመራሩም ሆነ የባለሙያ እገዛ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ልማቱን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋት ሥራ እንደሚከናወን አንስተው፤ ለዚህም የዲዛይን፣ መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነፃ የማድረግና ሃብት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት በሰባት ከተሞች 35 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ማከናወን እንደተቻለም አቶ ሽቤ ጨምረው አስታውሰዋል።