በሀላባ ዞን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በሀላባ ዞን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ
ቁሊቶ፤ ጥር 3/2018 (ኢዜአ) ፡- በሀላባ ዞን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
በዞኑ አስተዳደርና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተሰርተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት ነው ፡፡
የሀላባ ስታዲየም የመጀመሪያ ምዕራፍ ፕሮጀክት ግንባታ፣ የዞን አስተዳደር ህንጻና በአንድ ከተማ የአንድ ፕሮጀክት ኢንሼቲቭ አካል የሆነው የማህበረሰብ መድሃኒት ቤትና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉት መካከል ናቸው፡፡
ፕሮጀክቶቹ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን የተቀላጠፈ ለማድረግና ጤናማና አምራች ዜጎችን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ከማጠናከር በተጨማሪ የቁሊቶ ከተማን በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጉም ተገልጿል፡፡
ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች የመንግስትንና የማህበረሰብን አቅም አስተባብሮ በመጠቀም የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ እንደሚቻል በተጨባጭ ተሞክሮ የተወሰደበት ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የፕሮጀክቶቹ ምረቃ የተካሄደው የሀላባ ዘመን መለወጫ ‹‹ሴራ›› በዓል ከፌዴራል፣ ከክልልና ከተለያዩ መዋቅሮች የተገኙ ከፍተኛ አመራሮች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት እየተከበረ ባለበት ወቅት ነው፡፡