ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከ15 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ቡና ተመርቷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፡- በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከ15 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ቡና መመረቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

በተያዘው ዓመት 2 ሚሊየን 462 ሺህ 718 ሔክታር በቡና ልማት መሸፈኑን በባለሥልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፈቃዱ ደፈረስ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ አሁን ላይ ምርት የሚሰጥ የቡና መሬት ሽፋን በአርሶ አደር 1 ሚሊየን 537ሺህ 626 እንዲሁም በባለሃብት 143 ሺህ 140 ሔክታር መሆኑንም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ዘንድሮ የለማው መሬት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ20 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም ካለፉት ሥድስት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የ211 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አረጋግጠዋል።

በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት ከ15 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ቡና መመረቱን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 14 ነጥብ 37 ሚሊየን ኩንታል በአርሶ አደር ቀሪው በባለሃብት መመረቱን ገልጸዋል።

ይህም ካለፉት ሥድስት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከሦስት እጥፍ በላይ ብልጫ ማሳየቱን ነው ያስታወቁት።

ምርታማነትን በተመለከተም በባለሃብት 9 ነጥብ 9 እንዲሁም በአርሶ አደር ማሳ 9 ነጥብ 4 ኩንታል በሔክታር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቡና ምርታማነትንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ862 ሺህ ሔክታር በላይ ያረጁ ቡናዎች መታደሳቸውንና 9 ቢሊየን ችግኞች ገደማ መተከላቸውን ለአብነት አንስተዋል።

እንዲሁም በቡና እንክብካቤ ሥራ የተሻለ አፈፃፀም በመታየቱ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም 9 ሺህ 458 ኩንታል የቡና ምርጥ ዘር፣ 3 ነጥብ 15 ቢሊየን የቡና ችግኝ፣ 25 ሺህ ዲቃላ የቡና ችግኝ ባለፉት ሥድስት ወራት ብቻ ለተጠቃሚዎች መቅረቡን አብራርተዋል።

በቡና ማሳ ላይ የበሽታና ተባይ አሰሳ፣ የቡና ግንድ አድርቅ እና የቡና ፍሬ በሽታ መከላከል እንዲሁም የቡና አረም ቁጥጥር ተግባራት መከናወናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

#Ethiopian_News_Agency

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም