የኤፍኤ ካፕ ባለ ብዙ ክብሩ አርሰናል ከፖርትስማውዝ ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኤፍኤ ካፕ ባለ ብዙ ክብሩ አርሰናል ከፖርትስማውዝ ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ የሶስተኛ ዙር መርሃ ግብር ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በፍራተን ፓርክ ስታዲየም ፖርትስማውዝ ከአርሰናል ይጫወታሉ።
በእንግሊዝ ሁለተኛ ዲቪዚዮን (ሻምፒዮንሺፕ) የሚጫወተው ፖርትስማውዝ የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ነው።
አርሰናል 14 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው።
ሁለቱ ክለቦች በኤፍኤ ካፕ ሲገናኙ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አርሰናል ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
አርሰናል ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ግምት አግኝቷል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ከብራይተን ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በኦልትራፎርድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ዩናይትድ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን 13 ጊዜ አንስቷል። የብራይተን ትልቁ ውጤት እ.አ.አ በ1982/83 ለፍጻሜ ደርሶ በዛሬ ተጋጣሚው ተሸንፎ ዋንጫ ያጣበት አጋጣሚ ነው።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ በውድድሩ ተገናኝተው ማንችስተር ዩናይትድ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ብራይተን በዩናይትድ ላይ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ዌስትሃም ዩናይትድ ከኪውፒአር፣ ደርቢ ካውንቲ ከሊድስ ዩናይትድ እና ስዋንሲ ሲቲ ከዌስትብሮም ዛሬ ከሚደረጉ የኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ኤፍኤ ካፕ እ.አ.አ በ1871 መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
155 ዓመታትን ያስቆጠረው ኤፍኤ ካፕ የዓለም አንጋፋው የክለቦች ውድድር ነው።