ቀጥታ፡

ተጠባቂው የኤል ክሊሳኮ ደርቢ በስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፍጻሜ

አዲስ አበባ፤ጥር 3 / 2018 (ኢዜአ)፦በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ዛሬ የሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰዓት በሳዑዲ አረቢያ ኪንግ አብዱላህ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

ባርሴሎና በግማሽ ፍጻሜው አትሌቲኮ ቢልባኦን 5 ለ 0 እንዲሁም ሪያል ማድሪድ አትሌቲኮ ማድሪድን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።

የባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው።

ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ1902 ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ባርሴሎና 3 ለ 1 አሸንፏል።

ቡድኖቹ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ እስከ አሁን 303 ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተዋል።

ባርሴሎና 128 ጊዜ ሲያሸንፍ ሪያል ማድሪድ 111 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 64 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

ሁለቱ ክለቦች በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ለፍጻሜ ሲገናኙ የዛሬው ለ18ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 16 ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ ዘጠኝ ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።ባርሴሎና ስድስት ጊዜ ባለድል ሆኗል።

ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል (ውድድሩ የደርሶ መልስ ጨዋታ ፎርማት በነበረው ወቅት)።

አምና ሁለቱ ክለቦች በፍጻሜው ተገናኝተው ባርሴሎና 3 ለ 2 በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት መሆኑ የሚታወስ ነው።

ቡድኖች የስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለበርካታ ጊዜ ያነሱ ክለቦች ናቸው። ባርሴሎና 15 ጊዜ በማንሳት ቀዳሚነቱን ሲይዝ ሪያል ማድሪድ 13 ጊዜ አሸንፏል።

በጉዳይ ላይ የሚገኘው የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ኪሊያን እምባፔ በቡድኑ ስብስብ ውስ መካከቱ ለለሎስ ብላኮንሶቹ መልካም ዜና ሆኗል።

የ42 ዓመቱ ሆዜ ሉዊስ ሞንቴሮ የሁለቱን ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በስፔን ላሊጋ እና በስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በተመሳሳይ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም