ግብጽ የወቅቱን የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ኮትዲቯር በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀለች - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ የወቅቱን የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ኮትዲቯር በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀለች
አዲስ አበባ፤ ጥር 2 /2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ግብጽ ኮትዲቯርን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
ማምሻውን በአጋዲር ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኦማር ማርሙሽ፣ ራሚ ራቢያ እና መሐመድ ሳላህ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ጉዌላ ዱዌ እና የግብጹ አህመድ አቡ ኤል ፎቱህ በራሱ ላይ ለኮትዲቯር ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በጨዋታው ግብጽ ግልጽ የግብ እድሎችን በመፍጠር፣ ኮትዲቯር በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ነበሩ።
ኮትዲቯር በጨዋታው ማብቂያ ላይ ተጭና ብትጫወትም ግብ ማስቆጠር አልቻለችም።
የግብጹ መሐመድ ሳላህ በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ አራት ከፍ አድርጓል።
ድሉን ተከትሎ ግብጽ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጨረሻዋ ሀገር ሆናለች። በግማሽ ፍጻሜው ከሴኔጋል ጋር የምታደርገው ጨዋታ ከወዲሁ ትኩረትን ስቧል።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ክብሯን የመጠበቅ ጉዞዋ ሩብ ፍጻሜው ላይ ተገቷል።
በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ናይጄሪያ ከአዘጋጇ ሞሮኮ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ረቡዕ ጥር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳሉ።