ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፤ ጥር 2 /2018 (ኢዜአ)፦ 46ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ማምሻውን በአሜሪካ ፍሎሪዳ ተካሄዷል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በአምስት ርቀቶች በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 20 አትሌቶችን አሳትፋለች።

10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች፣ 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች፣ ከ20 ዓመት በታች ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር እና ድብልቅ ሪሌይ (4 በ 2 ኪሎ ሜትር) ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው ርቀቶች ናቸው።

የዛሬ ውድድሮችን ተከትሎ ኢትዮጵያ በሶስት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና ሁለት የነሐስ በድምሩ ሰባት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ኬንያን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የስድስት ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ማርታ ዓለማየሁ በ18 ደቂቃ 52 ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

ኢትዮጵያ በአዋቂ የ10 ኪሎ ሜትር ወንዶች እና ሶሴቶች በቡድን ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

በአዋቂ 10 ኪሎ ሜትር ወንድ ፍጻሜ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

አትሌት ወሰኔ አሰፋ ከ20 በታች ሴቶች የስድስት ኪሎ ሜትር ውድድር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

በ10 ኪሎ ሜትር ሴቶች አትሌት ሰናይት ጌታቸው እና በድብልቅ ሪሌይ (ዱላ ቅብብል)  የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል።

ኬንያ ሶስት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሁለት የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በማግኘት አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ዩጋንዳ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች። አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን እና አሜሪካ ሌሎች ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ሀገራት ናቸው።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮና ተሳትፎ ታሪኳ የዘንድሮውን ጨምሮ 112 የወርቅ፣ 123 ብር እና 67 የነሐስ በድምሩ 302 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከኬንያ በመቀጠል ስኬታማዋ ሀገር ናት።

ኬንያ የዘንድሮውን ጨምሮ ኬንያ 160 ወርቅ፣ 114 የብር እና 80 የነሐስ በድምሩ 354 ሜዳሊያዎችን በማግኘት የበላይነቱን ይዛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም