የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዲጂታላይዝ የሆነ አሰራሩን ማጠናከር ይገባዋል - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዲጂታላይዝ የሆነ አሰራሩን ማጠናከር ይገባዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የሪፎርም ስራዎችን በመተግበር አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ።
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢዎች እና ከምክር ቤቱ ሴቶች ኮከስ አመራር አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
ውይይቱም የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እያከናወናቸው በሚገኙ የሪፎርም እና የዲጂታል ስራዎች፣ የግዥና ንብረት የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም ወደፊት በትኩረት ሊሰራባቸው በታቀዱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ ፤ ባለስልጣኑ ሪፎርም ስራዎችን በመተግበር አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በመንግስት ግዥና ንብረት ዲጂታላይዜሽን፣ ከዘለቄታዊነት የግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት በማጎልበት ከመንግስት ግዥና ንብረት አገልግሎት እና መረጃ ጥራትና ሽፋን ለማሳደግ ያከናወነው ስራ ለሌሎችም ተቋማት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ እየተገበረ በሚገኘው ዘመናዊ አሰራር ከሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራትም ልምድ እያካፈለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመንግስት ግዥ ውጤታማ እንዲሆንና ግልጸኝነት ያለው አገልግሎት እንዲሳለጥ በማድረግ በኩል እያከናወነ ያለውን ተግባር ሊያጠናክር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በዘመናዊ አሰራር በመታገዝ የግዥ ስርዓቱን ለማዘመንና የቁጥጥር ስርዓቱን ከማጠናከር አኳያ በርካታ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከግዥ ጋር ተያይዞ ያለውን ግልጸኝነት ከማረጋገጥ እና ህገ-ወጥነት ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ዘመናዊ ስርዓቶችን መዘርጋቱን አብራርተዋል።
ባለስልጣኑ የአሰራር ስርዓቱን ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግ አዋጁን፣ መመሪያዎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ በማድረጉ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።
ለተገልጋዮች እና ለባለድርሻ አካላት ተከታታይ ሥልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል።
በተለይ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) ከፌዴራል ተቋማት አልፎ ወደ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የማውረድ ስራዎች ማከናወኑን ጠቁመዋል።
በውይይት የተሳተፉና አስተያየታቸውን የሰጡት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በበኩላቸው፤ ተቋሙ አሰራሩን ዘመናዊ እና ግልጸኝነት በማስፈን እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ እንደገለጹት፤ ተቋሙ አሰራሩን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው።
የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመንግስት ግዥ ስርዓት ግልጽና ፍትሃዊ እንዲሆን እየተደረገ ያለው የመቆጣጠር ስራ የሚበረታታ መሆኑን ነው የገለጹት።
ተቋሙ ከራሱ አልፎ ሌሎች ተቋማትን በዘመናዊ አሰራር ለማዘመን እያደረገ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንግስት ልማት ድርጅት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መለሰ መና በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት ያደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ በምክር ቤቱ የወጡ አዋጆችን በአግባቡ በመተግበር ለሌሎችም ተቋማት ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ የጀመረውን ተግባር በማጠናከር ለወደፊት የላቁ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አሳስበዋል።