የባህር ዳር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻነት የበለጠ ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻነት የበለጠ ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው
ባህርዳር ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻነት የበለጠ ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ አመራሮች በባህር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ዛሬ ማምሻውን ጎብኝተዋል።
የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊው ሰማ ጥሩነህ (ዶር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ የባህር ዳር ከተማን ይበልጥ በማዘመን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪውን በማስተባበር በኮሪደር ልማት፣ በስታዲየም ግንባታ፣ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ በአረንጓዴ ስፍራዎችና ሌሎች የልማት ስራዎች ያከናወነው የልማት ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ይህም ከተማዋን ከሀገር አቀፍና ከሌሎች የአለም ከተሞች ጋር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቧ ተወዳዳሪ እንድትሆን ማድረጉን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት፤ ከተማዋን የበለጠ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በከተማዋ እየተገነባ ያለው የኮሪደር ልማት ለኑሮ፣ ለመዝናኛና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።
ስማርት ባህርዳርን በመተግበር፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን እውን በማድረግ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አመራሮቹ የኮሪደር ልማት፣ አዲሱን የአባይ ድልድይ እንዲሁም በጣናነሽ ቁጥር 2 ጀልባ በጣና ሃይቅ ላይ ሽርሽር በማድረግ ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።