የሀላባ የዘመን መለወጫን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥናታዊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀላባ የዘመን መለወጫን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥናታዊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
ቁሊቶ፤ ጥር 2/2018 (ኢዜአ)፡- የሀላባ የዘመን መለወጫ (ሴራ) በዓልን በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚያግዙ ጥናታዊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ።
“ሴራ ባህላችን በኅብር የመቻል ዐቅም ማሳያች ነው” በሚል መሪ ሐሳብ በቁሊቶ ከተማ የሀላባ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ሲምፖዚዬም ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር በዚሁ ወቅት፤ የሀላባ ሴራ በዓል ከዘመን መለወጫ በዓልነት ባለፈ ማኅበረሰባዊ ትሥሥርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዲጠበቁና ለትውልድ እንዲተላለፉ በጥናት የተደገፈ ሠነድ አዘጋጅቷል ብለዋል።
የሀላባ የዘመን መለወጫ በዓል በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚያግዙ ጥናታዊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የሀላባ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ሙህዲን ሁሴን በበኩላቸው፤ የሴራ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሀላባ የዘመን መለወጫ በዓል የመጠያየቅና የመተጋገዝ ዕሴት የሚጠናከርበት መሆኑን የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ ይህን ለማስቀጠል መድረኩ ከፍተኛ ሚና ያበረክታል ብለዋል።