የስፖርት ቱሪዝምን በማጠናከር የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ቱሪዝምን በማጠናከር የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ ይገባል
ደብረ ብርሃን ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ የስፖርት ቱሪዝምን በመጠቀም በየአካባቢው ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የማስተዋወቅ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን ከተማ በነገው ዕለት በሚካሄደው የታላቁ ሩጫ ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የአንኮበር ቤተ መንግስትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት በቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አልቃድር አህመድ እንደገለጹት፤ በየአካባቢው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።ጉብኝቱም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ከቤተ መንግስት በተጨማሪ ተራራ የመውጣት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የስፖርት ቱሪዝምን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም በየአካባቢው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ሀላፊ ሃና ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ ታላቁ ሩጫ በአገራችን ያለውን የቱሪዝም ጸጋ በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
በዛሬው እለትም መነሻውን ከደብረ ብርሃን ከተማ ዘርዓያቆብ አደባባይ እስከ አንኮበር ቤተመንግስት የ42 ኪሎ ሜትር ጉዞ በማድረግ ጉብኝት ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
በነገው እለትም "ከአንኮበር እስከ ሀረር በር" በሚል መሪ ሃሳብ በስድስት የክልል ከተሞች የሚካሄደው የታላቁ ሩጫ የመጀመሪያ ዙር ሩጫ ውድድር በደብረ ብርሃን ከተማ ይካሄዳል ብለዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የአንኮበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይስማ ተክለፃዲቅ እንዳሉት፤ ወረዳው የቀደምት ነገስታት አብያተ መንግስታትና አስደናቂ መልክአ ምድር ያለው በመሆኑ ለጎብኚዎች ተመራጭ ነው።
ከደብረ ብርሃን እስከ አዋሽ አርባ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ መገንባቱ የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።