ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ይጠናከራሉ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በዲጂታል የታገዘ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የምግብ፣ መድሀኒትና የጤና አገልግሎት መስጠት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ የጤና ቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ "ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ለማይበገር የጤና ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ መከላከልን መሰረት ባደረገ የጤና ፖሊሲ የዜጎችን ጤናና ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶችን ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡


 

ይህ የጤና ፖሊሲ መከላከልን መሰረት ከማድረግ ባለፈ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ተደርጎ ተሻሽሏል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጥረት ማሳካት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የምግብ፣ የመድሀኒትና የጤና አገልግሎት ተደራሽ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተደረጉ የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎች የጤና ቁጥጥር ሂደቱን በማዘመን የማይበገር የጤና ሥርዓት መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከሶስት ዓመት በፊት የሀገር አቀፍ የመድሀኒት አቅርቦት በሀገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነው ስምንት በመቶ ብቻ እንደነበር በማንሳት፤ በአሁኑ ወቀት 60 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡

የጥራት መንደር ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማቅረብ የሚያስችል ተቋም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለሜዲካል ቱሪዝም መሰረት እንደሚጥልም ገልጸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት መሻሻል ፈዋሽነቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ ህክምና ከመስጠት ባለፈ ለሜዲካል ቱሪዝም የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል፡፡


 

አፍሪካውያን ለውጭ ህክምና አገልግሎት በዓመት እስከ አንድ ቢሊዬን ዶላር እንደሚያወጡ በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ባለችበት ጂኦ ስትራቴጂ የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል መሆን እንደምትችል ገልጸዋል፡፡

ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን አየር መንገድ እንደሚጠቀሙ በማንሳት፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት በመስጠት የሜዲካል ቱሪዝምን የሚያረጋግጡ ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማሳደግና ዲጂታል ስርዓትን ማዘመን እንደሚገባም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት 260 ሺህ የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች በብቃት ሰልጥነው መመረቃቸውን ገልጸው፣ ይህም የጤና ቁጥጥር ስርዓቱን ለማጠናከር ገንቢ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በጤናው ዘርፍ ያለውን ቁጥጥር በማጠናከር የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት የዲጂታል ስርዓት ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም