በዞኑ በልዩ ትኩረት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በልዩ ትኩረት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ነው
መቱ፤ ጥር 2/2018 (ኢዜአ)፡- በኢሉአባቦር ዞን በልዩ ትኩረት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ የግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አወል መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በያዝነው የበጋ ወራት በዋናነት የተቀናጀ የአፈርና ውኃ ጥበቃን ጨምሮ ችግኝ የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው።
በዚህም መሠረት 131 ሺህ ሔክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ሥራ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተፋሰስ ልማት በተሠራባቸው አካባቢዎች የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ችግኞቹ ለምግብነት፣ ለደን ልማት፣ ለከብቶች መኖና ለውበት የሚውሉ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።
የችግኝ ዝግጅቱ በመንግሥት ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ መካሄዱንም አስረድተዋል።
በመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞች ከአካባቢ ጥበቃ ፋይዳ ባለፈ በችግኝ ማፍላት ለሚሳተፉ ወገኖች የሥራ እድል እንደፈጠሩመ አክለዋል።
በችግኝ ማፍላት ሥራው የሥራ እድል ከተፈጠረላችው መካከል ሽብሩ አምቢሳ እንዳሉት፤ በችግኝ ጣቢያዎች ተቀጥረው ከሚያገኙት ገቢ ባሻገር በሥራው ያገኙትን ልምድ በግል ማሳቸው ላይ ለማስፋት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ችግኞችን ከማዘጋጀት ሥራ ጎን ለጎን ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ሥራም እያከናወኑ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር መተግበር ከጀመረ ወዲህ ችግኝ በማዘጋጀት ገቢ እያገኙበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አበራ ገለታ ናቸው።