ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል

ይርጋጨፌ፤ ጥር 2/2018 (ኢዜአ)፡- የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን የጌዴኦ ዞን አሥተዳደር ገለጸ።

በይርጋጨፌ ከተማ ሁለተኛው ዙር የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።


 

የጌዴኦ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዞኑ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተሞችን ገጽታ በመቀየር እድገታቸውን እያፋጠኑና ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ እያደረጉ ነው።

በዞኑ ዲላ፣ ይርጋጨፌና ወናጎን ጨምሮ በአምስት ከተሞች የተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራ የከተሞችን ደረጃ በማሻሻል ተወዳዳሪነታቸውን አሳድጓል ብለዋል።


 

በተለይም በጽዱ አካባቢ የመኖር ባህልን በማጎልበት ሕብረተሰቡ ለልማቱ ቅድሚያ እንዲሰጥ ማድረጉን አስገንዝበዋል።
 
ዛሬ በይርጋጨፌ የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራም የከተማዋን ውበትና ጽዳት በእጅጉ የሚያሳድግ መሆኑን አንስተዋል።

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የውኃ ብክለትን በመቀነስ ጤናው በተጠበቀ አካባቢ የመኖር ባህልን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለልማቱ ስኬት ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የሕብረተሰብ ተሳትፎ በተለይም የግል ባለሃብቶች ተሳትፎን በማጠናከር የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የኮሪደር ልማት ከተማዋን ምቹ ማድረጉን ያነሱት የይርጋጨፌ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ብዙአየሁ ታደሠ በበኩላቸው፤ ከተማዋን አቋርጠው የሚያልፉ ሦስት ወንዞች በአግባቡ ባለመያዛቸው ለብክለት መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

በፌጤ ወንዝ ላይ ዛሬ የተጀመረው ሁለተኛው ዙር የወንዝ ዳርቻ ልማት 750 ሜትር የእግረኛና የሳይክል መንገድ፣ የአረንጓዴ ስፍራና መዝናኛ ቦታዎችን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ማካተቱንም ጠቅሰዋል።

ይህም የወንዙን ብክለት በማስቀረት ለከተማው ተጨማሪ ውበትና እድገት የሚያጎናጸፍ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ሥራውን በቀጣይ ሥድስት ወራት አጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እንደሚደረግም ነው ያመላከቱት።

ሕብረተሰቡ ይዞታውን በማንሳት አጋርነቱን ማሳየቱን አንስተው፤ በልማቱም ተሳትፎውን ማጠናከር እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።


 

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል መላከሰላም ድረስ ታደሠ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ለወንዝ ዳርቻ ልማት ንብረታቸውን ማንሳታቸውን ተናግረው ልማቱ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የፌጤ ወንዝ በተለያዩ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች የተበከለ በመሆኑ ለጤና እክል ሲጋለጡ መቆየታቸውን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ታምራት ታደሠ ናቸው።

ዛሬ የወንዝ ዳርቻ ልማት ወደ ሥራ መግባቱ ብክለትን በማስቀረት ጽዱ አካባቢን ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም