የህግ ትምህርት ቤቱ የዘርፉን የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማሳደግ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህግ ትምህርት ቤቱ የዘርፉን የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማሳደግ እያገዘ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦የአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በዘርፉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርአያ ስላሴ ገለጹ።
ዛሬ በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤቱ 62ኛ አመት የምስረታ በዓል ተከብሯል።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት የሕግ ትምህርት ቤቱ በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ አስፈላጊ እውቀት እና ክህሎት የጨበጡ ተዋናዮችን በማፍራት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ከስድስት አስርት ዓመታት በበለጠ ጉዞው ዳኞች፣ አቃብያነ ህጎችና ጠበቆችን ጨምሮ በዘርፉ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርስቲውና ምሁራኑ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በመስራት የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ስራዎችን ጨምሮ የሕግ ማርቀቅ ተግባራት ላይም የላቀ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት።
በተለይም የህግ ትምህርት ቤቱ ምሁራን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት መስራታቸው ጥራት ያላቸው ህጎች እንዲወጡና ተግባራዊ እንዲደረጉ እያገዘ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በተጨማሪም በተቋሙ የሚሰሩ የዘርፉ ምሩቃን በትምህርት ቤት ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተጨባጭ በስራ ላይ እንዲያውሉ ለማድረግም በትብብር መስራቱ ሰፊ እገዛ ያለው መሆኑን ነው ያነሱት።
እንደ ሀገር የሕግ ትምህርት እና የሕግ ምርምር ላይ በቅንጅት መስራት የፍትሕ ስርዓቱን ጠንካራ ለማድረግ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ የፍትሕ ስርዓት እንዲቀረጽና እንዲተገበር በማድረግ ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የተናገሩት።
በተለይም የሕግ ትምህርትን ለማስፋፋትና በመላው ሃገሪቱ በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል ከማድረግ አንፃር ስኬታማ ስራዎችን መስራቱንም አመልክተዋል።
ባለፉት 62 ዓመታት ውስጥም 57 ዙር ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ባለሙያዎቹ ከሀገር ውስጥ ባለፈም በውጭ ሀገራት በዘርፉ የተሻለ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲን ፕሮፌሰር ሙራዱ አብዶ፤ የሕግ ትምህርት ቤቱ በዘርፉ የሰው ሀይል ከማፍራት በተጨማሪም ለማሕበረሰቡ ነፃ የህግ አገልግሎት በመስጠት ማሕበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በፍትሕ ስርዓቱ ዋና ተዋናይ የሆኑ ጠበቆች፣ዳኞች፣ተመራማሪዎችንና አማካሪዎችን በማፍራት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የፍትሕ ሚኒስትሯ ሀና አርአያ ስላሴን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እንዲሁም የቀድሞ ተማሪዎች ተገኝተዋል።