በሐረሪ ክልል በተፋሰስ ልማት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርትና ምርታማነትን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል በተፋሰስ ልማት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርትና ምርታማነትን አሳድጓል
ሐረር፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ባለፉት ዓመታት በተፋሰስ ልማት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርትና ምርታማነት ማሳደጉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር ገለጹ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ኡመር፤ የዘንድሮውን የክልሉን የተፋሰስ ልማት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በዛሬው እለት አስጀምረዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተጨባጭ ውጤት የተገኘበት መሆኑን አንስተው ዘንድሮም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በተለይም የከርሰ ምድር ውሃን በማጎልበትና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ልማት አጠቃቀም እና ጥበቃ ዳይሬክተር አራርሶ አደም፤ በክልሉ በዘንድሮ በጋ ወራት 9 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
በዚህም 300 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው እንደሚከናወን ጠቁመው በተፋሰስ ልማት ስራው ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የለሙ ተፋሰሶች የጎርፍ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባለፈ ለወጣቶች የስራ ዕድል እንደፈጠረም ገልጸዋል።