በክልሉ ለእናቶችና ህጻናት ጤና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለእናቶችና ህጻናት ጤና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተገኘ ነው
ባህር ዳር፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ለእናቶችና ህጻናት ጤና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተገኘ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው "ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት" በሚል መሪ ሃሳብ በጥር ወር የሚከበረውን የጤናማ እናትነት ወር አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ዛሬ ሰጥቷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትሜ እንደገለጹት ለእናቶችና ህጻናት ጤና ልዩ ትኩረት በመስጠት ጤናማ ትውልድ ለመገንባት እየተሰራ ይገኛል።
እስካሁን በተከናወኑ ስራዎችም ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የጤናማ እናትነት ወርን ምክንያት በማድረግ ሰፊ የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይሰራል ብለዋል።
በቀጣይም የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ባለሙያዎችን መመደብና አቅማቸውን ማሳደግ፣ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በግብአት ማሟላትና ማዘመን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 75 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመው ባለፉት ስድስት ወራት ከ305 ሺህ በላይ እናቶች በጤና ተቋማት መውለዳቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ከህክምና አገልግሎት አንጻርም በክልሉ ከሚገኙ 100 ሆስፒታሎች በተጨማሪ 36 ጤና ጣቢያዎች ለእናቶች የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም ያላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የቀዶ ህክምና አገልግሎቱን ወደ ሁሉም ጤና ጣቢያዎች ለማስፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።