የሀላባ የዘመን መለወጫ "ሴራ" ሲከበር የፍቅርና አብሮነት እሴትን በማጠናከር ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሀላባ የዘመን መለወጫ "ሴራ" ሲከበር የፍቅርና አብሮነት እሴትን በማጠናከር ሊሆን ይገባል
ቁሊቶ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ የሀላባ የዘመን መለወጫ "ሴራ" ሲከበር የፍቅርና አብሮነት እሴትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ መሀመድአሚን መህዲ ተናገሩ።
የ2018 የሀላባ የዘመን መለወጫ "ሴራ" በዓል "ሴራ ባህላችን በህብር የመቻል አቅም ማሳያችን ነው" በሚል መሪ ሀሳብ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አውደ ጥናት በቁሊቶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የሀላባ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መሀመድአሚን መህዲ፤ የሀላባ ሴራ አብሮነትን ማጠናከር፣ ቅራኔዎችን በይቅርታ መፍታት የሚያስችል የዳበረ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።
የ"ሴራ"በዓል ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲስ ዓመት የመሸጋገሪያና ለአቅመ አዳምና ሄዋን የደረሱ ወጣቶች የሚተጫጩበት ስርዓትን የያዘ መሆኑንም አንስተዋል።
በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የመደገጋፍና የአብሮነት እሴት የሚጠናከርበት፣ መሆኑን ተናግረው በዓሉ ሲከበር ጠብና ጥላቻን በእርቅና ይቅርታ በመሻር የፍቅርና አብሮነት እሴት በማጠናከር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የሀላባ የዘመን መለወጫ በዓል አከባበር እሴቱን ጠብቆ በማስቀጠል ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ የሀገር ሃብት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተዋል።
በመድረኩ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር ጨምሮ ሌሎችም የዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።