በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ ሃብት በተደመረ አቅም በማልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ ሃብት በተደመረ አቅም በማልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ ሃብት በተደመረ አቅም በማልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻልና ከድህነት ለመውጣት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት ክልሎች ባላቸው የልማት አቅም ወደ ምርታማነት እንዲገቡ ተደርጎ እስካሁን ስምንት ክልሎች የአደጋ ግዜ ምላሽን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠር ችለዋል።
ከእነዚህ ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ክልልን እንቅስቃሴ በተመለከተ ኢዜአ የክልሉን ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛን አነጋግሯል።
አቶ ሃይሉ በማብራሪያቸው በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ ሃብት በተደመረ አቅም በማልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገው ሽግግር ውጤት የመጣበት መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሙሉ አቅም መተግበር፣ ቡሳ ጎኖፋን ማጠናከር፣ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ተግባራዊ ማድረግ እና 'ጋቸና ሲርና' በተሰኘ መዋቅር ህዝቡ የራሱን ሰላምና ጸጥታ መጠበቅ እንዲችል ተደርጓል ብለዋል።
በተለይም ከገዳ ስርዓት የሚመነጨውና የኦሮሞ ህዝብ መረዳጃ ስርዓት የሆነውን ቡሳ ጎኖፋ ተግራዊ በማድረግ በራስ አቅም ችግሮችን የመቋቋም ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት አጋጥመው የነበሩ የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ቡሳ ጎኖፋ የእርስ በርስ መረዳጃ ስርዓት ብቻ ሳይሆን በመንግስት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለሚደረገው የሽግግር ጉዞ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ ማህበራዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል።
የአደጋ ምላሽን በራስ አቅም ለመወጣት በቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት በ2017/18 የምርት ዘመን ከ26ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቶ ምርት እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ መንግስት ከሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጎን ለጎን ህብረተሰቡ በበጎ ፈቃድ ስራዎች እንዲሳተፍ በማድረግ ትልቅ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ጀምሮ በእርስ በርስ መረዳዳትና በመተጋገዝ እንዲሁም በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ በኩል ስኬታማ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።።
ከዚህ አንጻር ከ2012ዓ.ም ጀምሮ እካሁን ከ20ሺህ በላይ 'ቡኡራ ቦሩ' የተሰኙ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በህዝብ ተሳትፎ ተገንብተዋል ብለዋል።
በተጨማሪም 59ሺህ በላይ የገጠር መምህራን መኖሪያ ቤቶችን መገንባት መቻሉን ጠቅሰው ህዝቡን የልማት ተሳታፊ ለማድረግ በተከናወነው ስራ ትልቅ ተሞክሮ የተወሰደበት መሆኑንም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ህዝቡ በራሱ ባህላዊ እሴት በመዳኘት ፈጣን ፍትህ በማግኘት ግዜውን ልማት ላይ እንዲያውል ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እስከ ቀበሌ ድረስ ተዘርግተው ተጨባጭ ውጤት እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል።