በወላይታ ዞን የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለስራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እገዛ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለስራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እገዛ እያደረጉ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለስራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ እገዛ እያደረጉ መሆኑን የዞኑ ንግድና ኢንዳስትሪ ልማት መምሪያ ገለጸ።
የወላይታ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይንሸት ሞላን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው።
በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ምክንያት ምርታማነታቸው የቀነሰና ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት በየደረጃው ከሚገኙ ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አንስተዋል።
በዚህም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከ1 ሺህ 24 በላይ አነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።
ተግባሩን በማጠናከርም ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ20 በላይ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ በመግባት ለስራ እድል ፈጠራና ተኪ ምርትን በማምረት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ዘርፉ ከፈጠረው የስራ ዕድል በተጨማሪ የዕውቀትና ክህሎት ሽግግር እንዲኖር ማስቻሉን ተናግረዋል።
በወላይታ ዞን ወደ ስራ በገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች እንዳሉት ኢንዱስትሪዎቹ የስራ እድልን ከመፍጠራቸው ባለፈ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ አግዘዋቸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የቦዲቲ ከተማ ነዋሪ ወጣት ፀጋዘአብ ዘሪሁን እንደገለጸው፤ በከተማው የታሸገ ውኃ በሚያመርት ፋብሪካ የስራ ዕድልን በማግኘቱ ራሱንና ቤተሰቦቹን እየደጎመ ነው።
በኢንዳስትሪው ያገኘው እድል ከአዲስ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቅ እድል እንደፈጠረለት አክሏል።
ከስራ እጥነት ወደ ስራና የሙያ ባለቤት የተቀየረው ሌላው የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ወጣት አሳምነው ዘሜ በበኩሉ፤ በተመረቀበት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በዱቄት ፋብሪካ ተቀጥሮ እየሰራ መሆኑን አንስቷል።
በፋብሪካው ካገኘው የስራ እድል ባለፈ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቅና ሙያውን እንዲያሳድግ እንዳገዘው ተናግሯል።