በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎች ለትውልድ ምንዳ ማውረስ የሚያስችሉ ናቸው -ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎች ለትውልድ ምንዳ ማውረስ የሚያስችሉ ናቸው -ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)
ባህር ዳር፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎች ለትውልድ ምንዳ ማውረስ የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ አመራሮች በተገኙበት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎች ለትውልድ ምንዳ ማውረስ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
ለዚህም ብልጽግና ፓርቲ ትናንትን፣ ከዛሬና ነገ ጋር አሰናስሎና አስተሳስሮ ለትውልድ ምንዳ ለማውረስ የሚያስችሉ ስኬታማ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
ፓርቲው በተለይም ባለፉት ዓመታት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የዲፕሎማሲ ድሎችን ማስመዝገቡን አንስተው ከተረጅነት የመውጣት ጥረትም ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
በግብርና ልማት፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ እና ሌሎችም ብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች የላቀ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።
በግንቦት ወር የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን ብልጽግና የድርሻውን ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጉንም ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፤ በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር በመቀልበስ ወደ ዘላቂ ሰላምና የተሟላ ልማት መገባት መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ በተለይም ለሰላም አማራጭ ትኩረት በመስጠት ስኬታማ ስራ መሰራቱን አንስተው የሰላምን አማራጭ በሚገፋ የጥፋት ቡድን ላይም የተጠናከረ ህግ የማስከበር እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል።
ለሁለት ቀናት የሚካሄደው መድረክ ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የስድስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ውይይት የሚደረግ መሆኑ ታውቋል።