ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሁሉም መስኮች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው ነው

ሰመራ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሁሉም መስኮች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ ተናገሩ።

"ጠንካራ አደረጃጀት ለጠንካራ ፓርቲ" በሚል መሪ ሀሳብ በብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 የ6 ወራት አፈፃፀም ግምገማ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ መድረክ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

መድረኩን ያስጀመሩት የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ እንዳሉት ፓርቲው የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።


 

እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ስራዎችም የብልፅግና አይቀሬነት እየተረጋገጠ መምጣቱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመትም ሀገርን ወደ ከፍታ ያሸጋገሩ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች የተፈጸሙበት እና ይፋ የተደረጉበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ የሆኑ አንፀባራቂ ስራዎች በተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው ይኼም ከተጠቃሚነት አኳያ የህብረተሰብን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሁሉም መስኮች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን ነው ያብራሩት።

በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ሁሉንም አኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።


 

በክልሉም ከዚህ በፊት ያልተለመዱ ሰፋፊ የግብርና ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በሰመራ ከተማም የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋን ለነዋሪው ጽዱ እና ምቹ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።


 

በክልሉ በተለይም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚደረገው ጉዞ ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወልኦ አይትሌ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም