ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቢሾፍቱ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በይፋ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቢሾፍቱ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ እምቅ አቅሟንና ታላቅ ርዕይዋን የሚመጥን ሌላ ተጨማሪ ሜጋ ፕሮጀክት ጀምራለች ሲል ገልጿል።

የቢሾፍቱ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት እንደሚሆንም አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የአውሮፕላን ማረፊያውን ግንባታ ይፋዊ በሆነ መርሃ ግብር ዛሬ በስፍራው ማስጀመራቸውንም አስታውቋል። 


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እለቱ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊነት እና ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ አንድ እጥፋት ነው በማለት እንደገለጹት ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የሀገር የኩራት ምንጭ መሆኑን አውስተው ይኽ የሆነው ግን ያለተግዳሮት በመጓዙ ሳይሆን በጽናት በተሞላው እንቅፋቶችን የመሻገር አቅሙ እና በአፍሪካ የፋና ወጊነት ሚናው የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ ትልቁ ጥንካሬ የሚመነጨው ከጠንካራው ተቋማዊ ባሕሉ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ማንሳታቸውንም አመልክቷል።


 

ለጥንቃቄ እና ደኅንነት ቅድሚያ መሥጠት፣ በፈጠራ እና ጠንካራ ሥራ የሚመራ አመራር፣ ከ26,000 በላይ ቁጥር ያለው በአየር መንገዱ ሰንደቅ ተሸካሚነት እና የሚወክለውን የሚያምኑ እና የሚያከብሩ ሠራተኞች እንዲሁም ያላሰለሰ የመማር እና የአቅም ግንባታ ጥረት የተቋሙ የትልቅ የጥንካሬ እና ጠንካራ ተቋማዊ ባህል እንዲገነባ ማስቻሉን መናገራቸውን አስታውቋል። 

ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ በ40 ኪሎሜትር ርቀት በ1910 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች የተመቸ ከባቢ ብሎም ኢትዮጵያን መዳረሻ ለሚያደርጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ምቹ አቀባበል የተመቸች እንደሚያደርጋት ነው ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀው።


 

ፕሮጀክቱ ብዛት ያላቸው የተሽከርካሪ መስመሮችን የያዘ አዲስ አበባን ከአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያገናኝ ዘመናዊ መንገድ ግንባታን ያካተተ ሲሆን በሰዓት ከ120-200 ኪሎ ሜትሮች ፍጥነት ያለው የከፍተኛ ፍጥነት የባቡር ሀዲድ እና ሥርዓት ግንባታንም አካትቷል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የቢሾፍቱ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚችል ሲሆን በታቀደው መሠረት ሙሉ ግንባታው በሚጠናቀቅበት ወቅትም በአመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል።

ይኽም ኢትዮጵያን ከአለም ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት ማዕከላት አንዷ እንደሚያደርጋት ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም