የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራን በብቃት በማከናወን ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራን በብቃት በማከናወን ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት ማድረግ ተችሏል
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018 (ኢዜአ)፦ የመዲናዋን ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ በብቃትና በልቀት በማከናወን ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ እየተገነቡ ከሚገኙ ስምንት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል የቀበና እና የግንፍሌ ወንዞችን የመስክ ምልከታ በማድረግ የሥራ ሂደቱን ገምግመዋል።
ከንቲባዋ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ የከተማዋ የወንዝ ዳርቻዎች ቀደም ሲል በቆሻሻ ክምችት የተሞሉ፣ በከባድ ጠረን ምክንያት ለመጠጋት የማይቻልበት ስፍራዎች ነበሩ።
ሆኖም አሁን ላይ ይሄ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ አካባቢው ውበት ተጎናፅፎ ለከተማችን ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ሆኗል ብለዋል።
ነዋሪዎች ንጹህ አየር የሚያገኙበት እና የሚዝናኑበት ምቹ አካባቢ መፈጠሩን አክለው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ለሕገ-ወጥ ተግባራት መሸሸጊያ የነበሩ ስፍራዎች አሁን ላይ ወደ ልማት በመቀየራቸው የነዋሪዎች ደህንነት መረጋገጡን ጠቁመዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በኢትዮጵያ አዲስ የልማት አይነት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ሥራው በብቃትና በልቀት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና አካባቢን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።
ደርቀው የነበሩ ምንጮች ዳግም መፍለቅ መጀመራቸውን አንስተው ልማቱ ተጨባጭ ውጤት እየታየበት መሆኑ ከንቲባዋ ጠቅሰዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማት ለሀገራችን አዲስ ተሞክሮ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂና ለውጥ አምጭ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱን ተከትሎ ባለሀብቶች በአካባቢው የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የቀበና ግንፍሌ ፒኮክ ፓርክ ወንዝ ዳርቻ ልማት የሚያስተባብሩት አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፤ አካባቢው ለረጅም ጊዜ በተለያየ መልኩ ሳይጠቅም የባከነና ትኩረት ተነፍጎት የቆየ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም አሁን ላይ በተከናወነው የተቀናጀ የጽዳትና የውበት ስራ ስፍራው ዳግም ህይወት ዘርቶ ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህም በቆሻሻ ተሸፍኖ የነበረውን እምቅ አቅም እንዴት ወደ ትልቅ ተስፋ መቀየር እንደሚቻል በተግባር የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።
ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለጎብኚዎች ማራኪ የመዝናኛ ስፍራ መሆኑን በማንሳት ለከተማዋ ደግሞ አዲስ የኢኮኖሚና የውበት ምንጭ እንደሆነ ገልፀዋል።
ይህ ስራ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን በትጋትና በቅንጅት ወደ ትልቅ ውጤት መቀየር እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ነው አቶ ሞገስ የገለጹት።