ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብር እና የኃይል ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብር እና የኃይል ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመገንባት ተምሳሌት ከመሆን ባለፈ ለቀጣናዊ ትብብር እና የኃይል ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድና በይቻላል መንፈስ እውን መሆኑ ይታወቃል።
ይህም ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ጎረቤት ሀገሮችን ጭምር በኃይል አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ ለአፍሪካ አንድነትና ትስስር ያላትን ሚና በማጎልበት በኩል የላቀ አበርክቶ አለው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢና የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ የሰሩት ታላቅ የአንድነት ገድል ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ አርአያ የሆነና ከቀኝ ግዛት እንዲውጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን አስታውሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ ዓድዋ ሁሉ የኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነት የተገለጠበት ከመሆኑ ባለፈ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም እውን ማድረግ እንደሚቻል ያሳየና ለአፍሪካ ሀገራትም ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ ነው ብለዋል።
ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ጭምር በኃይል አቅርቦት በማስተሳሰር ኢትዮጵያን ለአፍሪካ አንድነትና አብሮነት ወሳኝ የትብብር ማዕከል እንዳደረጋት ተናግረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር የሺ መብራት መርሻ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የትብብራችንና የአንድነታችን ውጤት ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገርን ሃብት ለልማት ማዋል የተቻለበት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአንድነትና በአብሮነት ትልቅ ተዓምር መስራት እንደሚቻል ሕዳሴ ግድብ ትልቅ ትምህርት የሰጠ በመሆኑ ትብብራችንን ማጠናከር ይኖርብናል ሲሉም አስገንዝበዋል።