ቀጥታ፡

ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርዓት በመፍጠር ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የምግብ የመድሀኒትና የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርዓት በመፍጠር ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የምግብ የመድሀኒትና የጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የጤና ቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ "ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ለማይበገር የጤና ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አንዱ መሳሪያ ነው።

ኢትዮጵያ መከላከልን መሰረት ባደረገ የጤና ፖሊሲ በዜጎች ጤናና ደህንነት ላይ አወንታዊ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።


 

ይህ የጤና ፖሊሲ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ የህክምና አገልግሎት መስጠት፣ የሀገር ውስጥ ምርት ጥራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም ከአራት ዓመት በፊት ስምንት በመቶ ብቻ የነበረውን የሀገር ውስጥ የመድሀኒት አቅርቦት ሽፋን ወደ 60 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በጤና ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ህጎች ላይ ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ሥርዓት በመፍጠር ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የምግብ፣ የመድሀኒትና የጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት መሻሻል ፈዋሽነቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ ህክምና ከመስጠት ባለፈ የውጭ ምንዛሪን በማዳን የጎላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርዓቱ ኢትዮጵያ በሜዲካል ቱሪዝም ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት 260ሺህ የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች በብቃት ሰልጥነው መመረቃቸውንና ለጤና ቁጥጥር ስርዓቱን ለማጠናከር ገንቢ ሚና አላቸው ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ ያለውን ቁጥጥር በማጠናከር የማይበገር የጤና ስርዓት መገንባት እንደሚገባ በማንሳት፣ የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማሳደግና ዲጂታል አሰራርን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም