የቢሾፍቱ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይሆናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይሆናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ የቢሾፍቱ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይሆናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮጵያን ፈጣን የአየር ትራንስፖርት እድገት እና እየሰፋ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ ትስስር ዘላቂ ለማድረግ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን በአመት የማስተናገድ አቅሙ ላይ ከደረሰው ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ አዲስ ሜጋ ጣቢያ እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይኽ የተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግምባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ አላማን ያነገበ ነው ብለዋል።
የቢሾፍቱ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።
ይኽም ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢንደስትሪ ማስፋፊያ አጀንዳ እና የረጅም ዘመን የአቪየሽን ስትራቴጂ ጋር የተናበበ መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያጠናክራል፤ በAfCFTA ማህቀፍ የአፍሪካን የማገናኘት አቅም ይጨምራል። የንግድ እና ቱሪዝም ኮሪደሮችን ያሰፋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህም ኢትዮጵያን ቀዳሚ የበይነ አኅጉር ማዕከል እንደሚያደርጋትም ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር አካባቢ የምትገኘውና 1910 ሜትር ከፍታ ያላት ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች ሥራ የተመቸ ከባቢ ያላት ሲሆን መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ላደረጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ብቁ ሁኔታ ያላት ናት ብለዋል።
ለመዲናችን ያላት ቅርበት ከነባሩ የአየር ትራንስፖርት ምኅዳር ጋር በቀላሉ የተዋሃደ አሠራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በአመት 60 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግድ ሲሆን ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከአለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መነኻሪያዎች አንዷ የሚያደርጋትን በአመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ላይ እንደሚደርስ ጠቁመዋል።