ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ8 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ8 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱን የሶማሌ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አሕመድ ረሺድ ገለጹ።

ፈቃድ የተሰጠው ለ51 ፕሮጀክቶች መሆኑንና 8 ቢሊየን 858 ሚሊየን 799 ሺህ ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውንም ኃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 705 ሚሊየን ብር ካፒታሉ በሥድስት የዳያስፖራ ባለሃብቶች የተመዘገበ መሆኑንም አስረድተዋል።

ፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ለ4ሺህ 31 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አስታውቀዋል።

አዳዲስ ፈቃድ የተሰጠባቸው ዘርፎችም ሆቴል፣ ግንባታ፣ አምራች ዘርፍ፣ ግብርና እና ትራንስፖርት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ለሁለት ባለሃብቶች የፕሮጀክት ማስፋፊያ ፈቃድ መሰጠቱንም ጨምረው አመላክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ውስጥ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እና የተመዘገበው ካፒታል ካለፉት ዓመታት አንጻር የተሻለ መሆኑንም አክለዋል።

ባለሃብቶች ሃብታቸውን በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉና የኢንቨስትመንት ልማቱ እንዲሳለጥ በክልሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው የማምረቻ፣ ለሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንቶች የግብርና መሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

ለፕሮጀክቶች አስፈላጊ የሆኑ የመሠረተ ልማት ዐውታሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ማመቻቸትና ያሉባቸውን ችግሮች በአፋጣኝ እልባት እንዲያገኙም በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማጠናከርና ግብርናውን ከአምራች ዘርፉ ጋር በማቀናጀት በዘርፉ ወጤታማ ተግባራትን በማከናወን ክልሉን የኢንዱስትሪ መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም