ቀጥታ፡

ወደ ቦረና የሚደረገው የአውሮፕላን በረራ መጨመር የጎብኚዎች ቁጥርን አሳድጓል

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018 (ኢዜአ)፡- ወደ ቦረና የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ እና የበረራ ቁጥሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር የቦረና ብሔራዊ  ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲያድግ ማስቻሉ ተገለጸ።

የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ዋርድ ንጉሴ ዋታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቦረና መብረሩ መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄ ከመቅረፉ በተጓዳኝ  የቱሪስቶች  ቁጥር  እንዲጨምር  ማስቻሉን አንስተዋል።

አየር መንገዱ ወደ ቦረና እያደረገ ያለውን የበረራ ቁጥር ሲጀምር ከነበረበት አሁን በሳምንት ወደ አራት ጊዜ ማሳደጉን ገልጸዋል።

ይህም ወደ አካባቢው የሚደረገውን የቱሪስቶች ቁጥር ከፍ እንዲል ማድረጉን ነው ያረጋገጡት።

የአየር ትራንስፖርቱ ምቹና ፈጣን በመሆኑ ጊዜያቸውን እንደቆጠበላቸው ቱሪስቶች መናገራቸውንም ገልጸዋል።

ለአብነትም በረራ ከተጀመረ ወዲህ ከ2 ሺህ በላይ ቱሪስቶችን ማስተናገዳቸውን ነው ያነሱት።

ፓርኩ ለጎብኚዎች ምቹ   ለመሆን እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፥ በአጭር ጊዜ የበርካቶች መዳረሻ መሆን መቻሉንም ጠቁመዋል።

በአጭር ጊዜ  የታየው አበረታች የጎብኚ ቁጥር በቀጣይ ትልቅ ተስፋ እንዳለ አመላካች ነው ብለዋል።

በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ፓርኩ የራሱን ሚና ያበረክታል ያሉት አቶ ንጉሴ፤ ለዚህም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም