ቀጥታ፡

አዘጋጇ ሞሮኮ ካሜሮንን በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ሞሮኮ ካሜሮንን 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ብራሂም ዲያዝ በ26ኛው እና ኢስማኤል ሳይባሪ በ74ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ዲያዝ በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ አምስት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነት አጠናክሯል።

የሪያል ማድሪዱ የክንፍ መስመር ተጫዋች በአምስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን አስቆጥሯል።

በጨዋታው ሞሮኮ ከፍተኛ ብልጫ ወስዳ ተጫውታለች።

ካሜሮን ኳስን መስርታ ለመጫወት ተቸግራለች። ግልጽ የግብ እድሎችንም መፍጠር አልቻለችም።

ጨዋታውን 64 ሺህ 178 ተመልካቾች ተከታትለውታል።

ውጤቱን ተከትሎ ሞሮኮ ግማሽ ፍጻሜ የገባች ሁለተኛ ሀገር ሆናለች።

በግማሽ ፍጻሜው ከአልጄሪያ እና ናይጄሪያ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

ሞሮኮ ለሁለት ዓመት ገደማ ሽንፈት ባለማስተናገድ በአስደናቂ ግስጋሴ ላይ ትገኛለች።

ዛሬ በተደረገው የመጀመሪያ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ሴኔጋል ማሊን 1 ለ 0 በማሸነፍ የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብታለች።

የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል አልጄሪያ ከናይጄሪያ፣ ኮትዲቯር ከግብጽ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም