ቀጥታ፡

ተጠባቂው የፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018 (ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ፋሲል ከነማ በሊጉ ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በ13ቱ ጨዋታዎች 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

በ25 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሽንፈት ያላስተናገደ ብቸኛው ክለብ ነው። በሊጉ አንስተኛ የግብ መጠን የተቆጠረበትም ቡድን ነው። 

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 13 ጨዋታዎች አከናውኖ በአራቱ አሸንፎ በስድስቱ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 11 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዷል።

ኢትዮጵያ ቡና በ15 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ጨዋታው ሁለቱ ክለቦች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

ፋሲል ከነማ ካሸነፈ ወደ ነበረበት ሁለተኛ ደረጃ ይመለሳል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ መድን ምሽት 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ወላይታ ድቻ እስከ አሁን በሊጉ ማሸነፍ የቻለው ጨዋታ ብዛት ሁለት ብቻ ነው። አምስት ጊዜ ሲሸነፍ ስድስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 16 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን 13 ጨዋታዎችን አድርጎ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በአራቱ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ግቦችን ተቆጥረውበታል። 

ኢትዮጵያ መድን በ13 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። 

መቻል ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። መቻል በ20 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። 

ባህር ዳር ከተማ በ16 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀድያ ሆሳዕና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ16 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ሀድያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 16 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም