ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት 46ኛው የዓለም አትሌቲክስ የሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት 46ኛው የዓለም አትሌቲክስ የሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ 46ኛው የዓለም አትሌቲክስ የሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ በአሜሪካ ታላሃስ ፍሎሪዳ ይደረጋል።
በሻምፒዮናው ላይ ከ52 ሀገራት የተወጣጡ 485 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
ኢትዮጵያም 20 አትሌቶችን በተለያዩ ርቀቶች ታሳትፋለች።
10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች፣ 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች፣ ከ20 ዓመት በታች ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር እና ድብልቅ ሪሌይ (4 በ 2 ኪሎ ሜትር) ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው ርቀቶች ናቸው።
በሪሁ አረጋዊ፣ ቢኒያም መሃሪ፣ በረከት ነጋ፣ መዝገቡ ስሜ፣ ንብረት ክንዴ እና ታደሰ ወርቁ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው።
በ10 ኪሎ ሜትር ሴቶች አሳየች አይቼው፣ አለሺኝ ባወቀ፣ ሹሬ ደምሴ፣ ሰናይት ጌታቸው፣ ለምለም ንብረት እና ዓለም ንጉስ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።
ከ20 ዓመት በታች ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር አየለ ሰውነት ይሳተፋል። ማርታ አለማየሁ፣ ወሰኔ አሰፋ እና የኔነሽ ሽመክት ከ20 ዓመት በታች ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው።
በድብልቅ ሪሌይ ሂሩት መሻሻ እና ገላ ሀምበሴ እንዲሁም ሚልኬሳ ፍቃዱ እና ወገኔ አዲሱ (ወንድ) ይሳተፋሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ለውድድሩ ለ47 ቀናት ዝግጅት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
አትሌቶቹ የተመረጡት በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም በተካሄደው 43ኛው ጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ባስመዘገቡት የተሻለ ውጤት ነው።
በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ፍሎሪዳ ማምራቱ ይታወቃል። ከዛ አስቀድሞ በሀገር ቤት ሽኝት ተደርጎለታል።
የዛሬ ውድድሮች በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 11 ሰዓት ከ45 አንስቶ ይካሄዳሉ።
የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ አትሌቶች ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል።
የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ እና ጃፓን አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአዋቂ ወንዶች እና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር የሚያሸንፉ አትሌቶች በተመሳሳይ የ30 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያገኛሉ።
በሁለቱም ጾታዎች የአዋቂ ውድድሮች አጠቃላይ የሚያሸንፉ ቡድኖች እያንዳንዳቸው ቡድኖች የ20 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
በድብልቅ ሪሌይ የሚያሸንፈው ሀገር 12 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንደሚያገኝ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2024 በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው 45ኛው የዓለም አትሌቲክስ የሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ፣ ስድስት የብር እና ሁለት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ኬንያን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮና ተሳትፎ ታሪኳ 109 የወርቅ፣ 121 ብር እና 65 የነሐስ በድምሩ 295 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከኬንያ በመቀጠል ስኬታማዋ ሀገር ናት።
ኬንያ 157 ወርቅ፣ 110 የብር እና 78 የነሐስ በድምሩ 345 ሜዳሊያዎችን በማግኘት የበላይነቱን ይዛለች።