የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር ከግብጽ የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል - ኢዜአ አማርኛ
የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር ከግብጽ የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቀሪ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ግብጽ ከኮትዲቯር በአጋዲር ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ግብጽ ቤኒንን፣ ኮትዲቯር ቡርኪናፋሶን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።
ከዚህ ቀደም ሀገራቱ በአፍሪካ ዋንጫው አራት ጊዜ ተገናኝተዋል።
ግብጽ እ.እ.አ. በ2006 ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፍጻሜው ኮትዲቯር ጋር በፍጻሜው ተገናኝታ በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ቡድኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተገናኙት ሱዳን እ.አ.አ በ1970 ባዘጋጀችው ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው።
ሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ ባደረጉት ጨዋታ ግብጽ 3 ለ 1 በማሸነፍ ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች።
ግብጽ ከኮትዲቯር ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ያደረገቻቸውን አራት ጨዋታዎች አሸንፋለች።
በዘንድሮው አፍሪካ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙት ሀገራት ጠንካራ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
መሐመድ ሳላህ እና ኦማር ማርሙሽ ከግብጽ፣ አማድ ዲያሎ እና ፍራንክ ኬሲዬ ከኮትዲቯር በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው ግምት ያገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ክብሯን ለማስጠበቅ የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋን ግብጽን ማሸነፍ ይጠበቅባታል።
የሁለቱ ሀገራት አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከሴኔጋል ጋር ይጫወታል።
በሌላኛው የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር አልጄሪያ ከናይጄሪያ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በማራካሽ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በጥሎ ማለፉ አልጄሪያ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን፣ ናይጄሪያ ሞዛምቢክን በማሸነፍ ስምንት ውስጥ ገብተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለ10ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አልጄሪያ አራት ጊዜ ስታሸንፍ ናይጄሪያ ሶስት ጊዜ ድል ቀንቷታል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ከዘጠኙ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱ በፍጻሜ የተገናኙባቸው ናቸው።
ናይጄሪያ እ.አ.አ በ1980 ባዘጋጀችው 12ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፍጻሜው አልጄሪያን 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ፓትሪክ ኦሊሴጉን ኦዴግባሚ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሙዳሺሩ ባባቱንዴ ላዋል ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
እ.አ.አ በ1990 በአልጄሪያ በተካሄደው 17ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ሀገር በፍጻሜው ናይጄሪያን በቼሪፍ ኡጃኒ ግብ 1 ለ 0 በመርታት ዋንጫውን ከፍ አድርጋለች።
ሀገራቱ ለመጨረሻ ጊዜ በአህጉራዊው መድረክ የተገናኙት እ.አ.አ 2019 ግብጽ ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው ሲሆን አልጄሪያ 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜው አልፋለች። አልጄሪያ በፍጻሜው ሴኔጋልን በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን አንስታለች።
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ያሸነፉት ሁለቱ ሀገራት በዛሬው መርሃ ግብር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጨዋታው አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከሞሮኮ ጋር ይገናኛል።
ትናንት በተደረጉ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሴኔጋል እና አዘጋጇ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።