ሴኔጋል ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች - ኢዜአ አማርኛ
ሴኔጋል ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ሴኔጋል ማሊን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ማምሻውን በታንጀር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢሊማን ንጃይ በ27ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
የማሊው አምበል ይቪስ ቢሱማ በሁለት ቢጫ በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ይህም ማሊን በሁለተኛው አጋማሽ በ10 ተጫዋች እንድትጨርስ አስገድዷታል።
ማሊ በውድድሩ በአጠቃላይ ሶስተኛ ቀይ ካርድ ያገኘች ሲሆን በዚህም ከፍተኛውን ቀይ ካርድ የተመለከተች ሀገር ሆናለች።
ከቀይ ካርዱ በፊት በጨዋታው ብልጫ ወስዳ የተጫወተችው ሴኔጋል የቁጥር ብልጫው ጨዋታውን የበለጠ እንድትቆጣጠር አስችሏታል።
ውጤቱን ተከትሎ ሴኔጋል ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለች የመጀመሪያ ሀገር ሆናለች።
በግማሽ ፍጻሜው ከኮትዲቯር እና ግብጽ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ካሜሮን ከአዘጋጇ ሞሮኮ ጋር በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።