በመዲናዋ እየተገነባ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ የልማትና የግንባታ እሳቤን ዕውን ያደረገ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ እየተገነባ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ የልማትና የግንባታ እሳቤን ዕውን ያደረገ ፕሮጀክት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት አዲስ የልማትና የግንባታ እሳቤን ዕውን ያደረገ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጫ ፕሮጀክት መሆኑን አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
ፕሮጀክቱ የተፈጥሮ ሃብት ህልውናን በመጠበቅ የከተማዋን ገጽታና ደረጃ ለማሳደግም አይነተኛ አበርክቶ ያለው መሆኑን ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ከሚገኙ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የቀበናና ግንፍሌ ወንዞች ልማት ሂደትን ገምግመዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ወንዞቹና ዳርቻዎቻቸውን ከስጋትነት አላቆ የተሻለ የከተማ ስነምህዳርና ገጽታ ያላበሰ የዛሬ ትውልድ ታላቅ አሻራ ነው ብለዋል ከንቲባዋ፡፡
እነዚሁ ፕሮጀክቶችም የአዲስ አበባን ስነምህዳር በዘላቂነት እንዲጠበቅ ከማድረግ አልፈው የነገ የከተማዋ ፍላጎትና የቤት ስራዎችን ታሳቢ ያደረጉ ተጨማሪ ልማቶችን ያካተቱ መሆናቸውንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
ፊት የማይሰጣቸውና ለልማት የተገለሉ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ ላይ የብዙዎች አይን ማረፊያ ምቹ የአገልግሎት መስጫ ማእከላት ሆነው መልማታቸውን የገለፁት ከንቲባዋ አልሚዎችና ባለሃብቶች እነዚህን የለሙ ስፍራዎች ይጠቀሙባቸው ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለአዲስ አበባም ለሀገርም አዲስ ደግሞም ምሳሌ የሆነው ወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን ህልውና በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር የከተማዋን ከስሟ የመስተካከል ትጋትን ለማሳለጥ የሚያግዝ ውጤት እየተገኘበት ስለመሆኑ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
8 ዋና ዋና የአዲስ አበባ ወንዞችን ያቀፈው 48 ኪሎሜትር የሚሸፍነው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ያስታወቁት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የግንባታ ሂደቱን እያስተባበሩ ላሉ አመራሮች በግንባታው እየተሳተፉ ላሉ ሰራተኞች እንዲሁም ድጋፍ እያደረጉ ላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በከተማዋ እየተገነቡ ካሉ 8 የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የቀበና ግንፍሌ ፒኮክ ፓርክ ወንዝ ዳርቻ ልማት የሚያስተባብሩት የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ ቁልቁል ከተማዋን እየከፈለ በሚሄደው የቀበና ወንዝ ዳርቻ እየተጠናቀቀ ያለው ልማት ከውሃ ሃብት ጥበቃ ስራ ባሻገር ተጨማሪ አገልግሎት መስጫ የገቢ ማስገኛ አማራጮች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ትላንት የሚያስቆጭ ነገን የሚያስናፍቅ ብርታትና ተስፋን የሚያሰንቅ ነው ብለዋል የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ሞገስ፡፡
የአዲስ አበባ ወንዝ ተጎራባች ስፍራዎች ለተፈጥሮ ሃብቱ ስጋት ሆነው ለዘመናት ከመዝለቃቸው በላይ ለነዋሪዎቹ የሰቀቀን ህይወትን ለመግፋት ሰበብ የነበሩ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ላይ በወንዝ ዳርቻ ልማት ተፈጥሮም ህይወትም ዳግም ህይወት ዘርተዋል፡፡