ቀጥታ፡

የማሌ የዘመን መለወጫ በዓል የእርስ በርስ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ አበርክቶ አለው

ጂንካ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦የማሌ የዘመን መለወጫ በዓል "ዶኦሞ" እሴት የህዝብን የእርስ በርስ ትስስር በማጠናከር ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተገለጸ።

የማሌ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ "ዶኦሞ" በዓል በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ በሌሞጌንቶ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፣ "ዶኦሞ" የአንድነት፣ የሰላምና የወንድማማችነት ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዓሉ አብሮነትን በማጠናከር ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል።


 

የበዓሉ መከበር የማሌዎች ባህላዊ እሴቶችንና ያሏቸውን ታሪካዊ ቅርሶች ለትውልድ ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል። 

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው፤ የማሌ የዘመን መለወጫ በዓል "ዶኦሞ" የህዝብን የእርስ በርስ ትስስር፣ አብሮነትና ሰላምን የሚያጠናክሩ እሴቶች አሉት።


 

የበዓሉን እሴቶች በጥናትና ምርምር ከማሳደግ ባለፈ በዓሉን ለማስተዋወቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ  ተናግረዋል።

ማሌዎች የራሳቸው የጊዜ ቀመርና አቆጣጠር እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ የማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አልጋጋ ባልንሴ ናቸው፡፡


 

በዓሉ በየዓመቱ ጥር 1 ቀን ወይም በብሄረሰቡ አጠራር "ባሬ ፔቴ" ተብሎ በሚጠራው ወር የሚከበር ሲሆን፣ በዓሉም ባለፈው ዓመት ለሆነው መልካም ነገር ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው።

በተጨማሪም መጪው አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤናና የአብሮነት እንዲሆን ፈጣሪን በመማፀን ያከብሩታል።

በዛሬው እለትም በዓሉ "የዶኦሞ ብስራት ለአንድነትና ለዕድገት" በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይትና በተለያዩ ባህላዊ ሥርአቶች መከበሩን አመልክተዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ በየደረጃው ያሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የእምነት አባቶች መገኘታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም