አርሶ አደሮች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በለሙ ተፋሰሶች ላይ ጥምር ግብርናን በመተግበር ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሮች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በለሙ ተፋሰሶች ላይ ጥምር ግብርናን በመተግበር ተጠቃሚ ሆነዋል
ደብረ ብርሃን ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በለሙ ተፋሰሶች ላይ ጥምር ግብርናን በማከናወን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን የደብረ ብርሃን አርሶ አደሮች ገለጹ።
በእቴጌ ጣይቱ ከፍለ ከተማ የሳሪያ ቀበሌ አርሶ አደር ወሰኔ ሰይፈ፤ ባለፉት ዓመታት በአፈርና ውሃ ጥበቃ በለሙ ተፋሰሶች ላይ በእንስሳት መኖ ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ሌሎች ልማቶች ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በዓመት በአማካይ ከ80 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደቻሉም ገልፀዋል።
ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተክልየ አይተፍሱ በበኩላቸው፤ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ በክረምቱ ጥምር ጥቅም የሚሰጡ የጌሾ፣ የባህር ዛፍና ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ መርሻ አይሳነው እንደገለጹት፤ በአካባቢው ተራቁቶ የነበረው መሬት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አገግሟል።
በዚህም የከርሰ ምድርና ገፀ-ምድር ውሃ ሀብት በመጨመሩ አካባቢው በልምላሜ መሸፈኑንና ምርታማነት ማደጉን አንስተዋል።
ይህም አርሶ አደሩ በመስኖና በመኖ ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በአትክትልና ፍራፍሬ ልማት በመሰማራት ተጨማሪ ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው በጋም በ45 ተፋሰሶች በአንድ ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መጀመሩን አስረድተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በበኩላቸው፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የኢንዱስትሪ ልማት እየተስፋፋባት ለምትገኘው ከተማ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ይህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ደኖችን ለማልማት፣ ከኢንዱስትሪው የሚወጣውን በካይ ጋዝ ለመቀነስና የአካባቢውን ልማት ለማሳደግ መሰረት እንደሚጥል ጠቁመዋል።