በድሬዳዋ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተመዘገቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተመዘገቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ድሬዳዋ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተመዘገቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
የአስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት እና የሴክተር ተቋማት የግማሽ በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ዛሬ ተገምግሟል።
የግምገማውን መድረክ የመሩት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት፤ በግማሽ በጀት ዓመት የህዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው።
በዘንድሮ በጀት ዓመት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ተግባር በማሸጋገር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
ይሄን ውጤታማ ስራ በማጠናከርና በማስፋት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ርብርቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለፃ ፤በአስተዳደሩ የገጠሩን ማህበረሰብ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር እና የከተማውን የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት ጥያቄዎች ለማቃለል የተሰሩ ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በግማሽ በጀት ዓመቱ የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ 167 ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜና ጥራት ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት እየተከናወኑ የሚገኙት የኮሪደር ልማት እና የተለያዩ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ድሬዳዋን የምስራቁ የሀገራችን ክፍል ተመራጭ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረጉ ጉዞን እያሳኩ መሆኑን ተናግረዋል።
እየተሰሩ የሚገኙት ልማቶች ድሬዳዋን ፅዱና ውብ የኑሮና የስራ ማዕከል ማድረጋቸውን በመጠቆም እነዚህን ስራዎች በላቀ ቅንጅትና ርብርብ ከዳር የማድረሱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የተሳተፉት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ዘርፎች አማካሪዎች ፍቃዱ በየነ (ዶ/ር) እና ሰይፉ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በግማሽ በጀት ዓመቱ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በጤናና በትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ላይ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።
በቀሪው ግማሽ በጀት ዓመት የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ገቢን እና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የተጀመሩትን ስራዎች በላቀ ጥራትና ውጤት ዳር ማድረስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል።
የሴክተር ተቋማት አመራሮች በበኩላቸው፤ በግማሽ በጀት ዓመቱ የተከናወኑት የልማት ስራዎችን በማሳደግ እና ክፍተቶችን በማረም የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በቁርጠኝነት እንደሚተጉ አረጋግጠዋል።