በክልሉ የምጥን መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የምጥን መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በእንስሳት ልማት ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የምጥን መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና አሣ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ነጋ ይስማው እንደገለጹት፤ የእንስሳት ሃብትን አልምቶ ለአገር እድገት ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ዘርፉን በማዘመንና ሳይንሳዊ አሰራርን በመከተል ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለስርአተ ምግብ መሻሻልና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለእንስሳት ልማት ማነቆ የሆነውን የመኖ እጥረት ችግር ለመፍታት በክልሉ የሚገኙ 42 የመኖ ማቀነባበሪያዎችን በማጠናከርና በመደገፍ ምጥን መኖን በብዛትና በጥራት እንዲያመርቱ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በጎንደር፣ በወልዲያ፣ በደብረ ብርሀን ከተሞችና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ተጨማሪ የምጥን መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምጥን መኖ በተጨማሪ በእንስሳት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች፣ ማህበራትና ግለሰቦች ባላቸው መሬት ላይ የመኖ በቆሎ በመዝራት አረንጓዴነቱን ሳይለቅ የገፈራ መኖ አዘጋጅተው እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የእንስሳት መኖ ልማት ሥራው በክልሉ ያለውን የሥጋ፣ የወተት፣ የእንቁላል፣ የአሣና የማር ምርትን በእጅጉ ከማሳደግ ባሻገር የምግብ ንጠረ ነገሮችን ለመጨመር የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዝርያ ማሻሻል፣ በግብአት አቅርቦትና በቴክኖሎጂ ተደራሽነት ላይ በማተኮር የእንስሳት ዘርፉን ለማዘመን ቁርጠኛ አቋም ተወስዷል ብለዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በዘመናዊ እንስሳት ልማት የባህር ዳር ከተማን ለሌሎች የክልሉ ከተሞች የሰርቶ ማሳያ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በማህበራት፣ በግለሰቦችና በባለሃብቶች በተበታተነ መንገድ ሲካሄድ የነበረውን የዶሮ፣ የእንስሳት ማድለብ፣ የወተት፣ የአሣ እና የንብ ማነብ ልማት በክላስተር እንዲሰራ መደረጉን አስረድተዋል።
ለዚህም አስተዳደሩ ለእንስሳት ማድለብ፣ ለወተት ልማትና ለዶሮ መንደር ግንባታ የሚውል ከ32 ሄክታር በላይ መሬት ማዘጋጀቱን ጠቁመው፣ ለሼድ ግንባታም 50 ሚሊዮን ብር መድቦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በወተትና ዶሮ ልማት ሞዴል ሼድ በማስገንባት በቀጣይ ሌሎች ሼዶችን በመገንባት በባለሃብቶች፣ በግብረሰናይ ድርጅቶችና ሌሎች አካላት እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል።
ይህም ከተማዋን በወተት፣ በሥጋ፣ በእንቁላል፣ በማርና አሣ ምርት ውጤታማ በማድረግ ለሌሎች የክልሉ ከተሞች ማሳያ ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳለጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጎሹ ገለጻ፤ በዓባይ ወንዝና በጣና ሐይቅ ዳርቻ አካባቢዎች የሚከናወን የተፋሰስ ልማት ሥራ ወንዙንና ሐይቁን ከብክለትና ከደለል ከመከላከል ባለፈ ለእንስሳት መኖ ለማምረት እያስቻለ ነው።
በአማራ ክልል 37 ሚሊዮን የሚጠጋ የዳልጋ ከብት፣ በግና ፍየል እንዲሁም 20 ሚሊዮን የሚጠጋ የዶሮ ሃብት እንደሚገኝ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።